የጅቡቲ ወደብ የስራ ኃላፊዎች የ“ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ኤግዚቪሽንን ጎበኙ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዴንጌ ቦሩ የወደቡን የስራ ኃላፊዎች ተቀብለው አስጎብኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ምሳሌ በሚሆን መልኩ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አረንጓዴ ትራንስፖርትን በማስፋፋት ከተሸከርካሪዎች የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለማስቀረትና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን በቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን ከነዳጅ በማላቀቅና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያሥችል የትራንስፖርት ስርዓት በመገንባት ላይ ትገኛለች ሲሉ ሚኒስት ዴኤታው አክለዋል፡፡

በተጨማሪም ይህንን የአረንጓዴ ትራንስፖርት ለማስፋፋት የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎችና ባለድርሻ አካላትን ትብብር ለማጠናከር ታስቦ ኤግዚቪሽኑ መዘጋጀቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ጃማ ኢብራሄም የጅቡቲ ዶራሌ ወደብ ስራ አስኪያጅ የ“ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ኤግዚቪሽንን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት የጀመረችው ስራ የሚበረታታ ነው ፡፡

የአረንጓዴ ትራንስፖርት ጅማሮ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ረገድ ለአፍሪካም ሆነ ለመላው ዓለም ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አንሰንተው ኢትዮጵያ የወሰደችው ቁርጠኝነት ያስመሰግናታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በርካታ የሆኑ የጋራ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን አንስተው በጅቡቲ ወደብ በኩል በሚሰጡ አገልግሎቶች ሁሉ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ግንባታ ግቧን እንድታሳካ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የወደቡ ስራ ኃላፊዎች በኤግዚቪሽኑ የቀረቡ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የብዙሃን ትራንስፖርት፣ አውቶሞቢሎች፣ የመለስተኛ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ብስክሌቶችና ሌሎችም አረንጓዴ ትራንስፖርት አነስተኛ የአረንጓዴ ትራንስፖርት አማራጮችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

Share this Post