በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚመጥን የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያሥፈልግ ተገለፀ፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚመጥን የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያሥፈልግ ተገለፀ፡፡
መስከረም 23/2017 ዓ.ም (ትሎሚ)፡- በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚመጥን የባቡርና የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያሥፈልግ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የባቡር ትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ዘርፉን ብቁና ውጤታማ ለማድረግ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ለመፍጠር በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ነው፡፡
ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሎጂስቲክስ ዘርፉ ወሳኙን ሚና ይጫወታል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
የባቡር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አሰራርን በማዘመንና የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት እያደገ የመጣውን የወጪ እና ገቢ ንግድ በማሳለጥ ኢትጵያን በሎጂስቲክስ ዘርፉ ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት በመቀናጀትና የግል ዘርፉን በስፋት ማሳተፍ የሚያስችል የሪፎርም ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ውጤታማ የሆነ ሎጂስቲክስ ሥርዓት የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት ከመሆኑም በተጨማሪ ቀጠናዊና ዓለምአቀፋዊ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡
የአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተለወጠ ባለው ዓለም አቀፋዊ የሎጂስቲክስ ስርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘርፉን ማዘመንና ተገቢ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሎጂስቲክስ ስርዓት የማሳደግ እንቅስቃሴን ውጤታማ ለማድረግ ዓለም ባንክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዴንጌ ቦሩ በበኩላቸዉ እየተሰራ ያለውን የባቡርና የሎጂስቲክስ ሪፎርም ዓላማ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንና መወሰድ ያለባቸውን መፍትሔዎች አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ ተወካዮች እና ሌሎችም ባቡርና የሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ድርሻ ያላቸው ተቋት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በዌ ብሳይቱ Resources ላይ በመግባት Rail Reform 2024 ማግኘት ይችላሉ (MOTL)