“ለበርካታ ዓመታት ሊመነዘር የሚችል ውጤት በሰባት ዓመታት ብቻ የተመዘገበው ኢትዮጵያ ብቃት ያለው መሪ ስላገኘች ነው፡፡” ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ

የብልፅግና ፓርቲ የትራንስፖርት እና ሎጂስክስ ወረዳ ባለፉት 7 የለውጥ አመታት የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ “ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቃሉን የሚኖር፣ ሀሳብ ያለውና በተግባር የሚገለጥ መሪ ስላገኘች በሰባት ዓመታት ውስጥ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

መጋቢት 24/2010 ዓ.ም የዜሮ ድምር ፖለቲካ በር የተዘጋበት፤ የሃሳብ ልዕልና በር የተከፈተበት፤ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ርብርብ የተጀመረበት፤ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግርና ስርዓት በሰላማዊ መንገድ እንዲቀየር መሰረት የተጣለበት ነው ብለዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁሉም ማንነቶች የሚሳተፉበት ስርዓት በመገንባት የዜጎችን የዘመናት ጥያቄ መልሰዋል ሲሉም አክለው ተናግረዋል፡፡

የሃሳብ ልዕልና ቦታ እንዲይዝ፤ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ስልጣን በህዝብ ይሁንታ ብቻ እንዲሆን ዜጎች ዋጋ ሲከፍሉ የቆዩ ቢሆንም የኢትጵያውያን ምኞች እውን የሆነው ግን ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከራስ በላይ ለሀገርና ለህዝብ የሚያስብና ሀገርን ሊያሻግር የሚችል መሪ ስላልነበራት የዜጎች መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ቆይተዋል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ባለፉት ሰባት ዓመታት አሳታፊነት፣ አካታችነትና ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ያደረጉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

የተቋማት የለውጥ ስራዎች፣ የምርት እድገት፣ የትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እውን መሆንና ሀገራችን በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ የተቻለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ሀሳብ አምንጭነት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በተለይም በተከተልነው ጠንካራ ዲፕሎማሲ የሀገራችን የባህር በር ጥያቄ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ የተቻለ ሲሆን ይህም መሪያችን የጀመረውን በስኬት የሚጨርስ በመሆኑ እውን እንደሚሆን እንተማመናለን ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ተቋማትን በማጠናከር የሴክተሩን ሁለንተናዊ ለውጥ በማረጋገጥ የዘመነ ተቋም ለልጆቻችን ማውረስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገር ከሴክተራችን የምትጠብቀውን ለውጥ ለማምጣት ጠንክረን በመስራት ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን እውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት የታዩ ለውጦች በጠቅላይ ሚኒስትራችን በሳል አመራርና ቁርጠኝነት የመጡ መሆናቸውን አስታውሰው ለውጦችን ለማስቀጠል የሁላችንም ዝግጁነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በተሰጠን ኃላፊነት ብቁ ሆኖ በመገኘትና ውጤታማ ስራ በመስራት የኢትጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ መትጋት አለብን ብለዋል፡፡

እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ በመቀራረብ፣ አስተሳሳሪና የጋራ ትርክትን በመገንባት አንድነታችንን እናጠናክር ሲሉም መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Share this Post