አቶ ታገሰ ጫፎ የኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕይን በይፋ ከፈቱ
በአረንጓዴ ትራንስፖርት እና በታዳሽ ሀይል መሠረት ልማት ላይ ትኩረትን ያደረገው ይህ ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሁዋንጃን የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው የተከፈተው።
የኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመገንባት በሁሉም ዘርፎች የተጀመረው ሥራዎችን ለማስቀጠል በትራንስፖርት ዘርፍ የተጀመረው ተግባራት ይደግፋል ተብሏል።
ክቡር ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው በኤሌክትሪክ እና በታዳሽ ሀይል የሚሰሩ ተሸከርካዎችን መጠቀም በካርበን ልቀትን ለመቀነስ እና በከተሞች የትራፊክ ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ በማህበረሰቡ ጤናማ የሆነ የአኗኗር ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እና እንደ ሀገር ለዜጎች እኩል ተጠቃሚነትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መፅኢ ጊዜን እውን ለማድረግ ከታለሙ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ሀገራችን ወደ ላቀ ልማት ለምታደርገው ጉልህ የሆነ ምዕራፍ በአረንጓዴ ሞቢሊቲን ለማሳደግ ዓለም ላይ ለሚያደርገው ርብርብ አስተዋጽኦ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በመርኃ ግብሩ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተገኝተዋል፡፡
በዓውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየም ላይ ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሰረተ ልማት አምራች ድርጅቶች፣የተለያዩ የመንግስት የግል ተቋማት ስራቸውን ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ምርታቸውን እና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል፡፡
በዓውደ ርዕይ እና ሲምፖዚየሙ ከህዳር13-20/2017 ዓ.ም ድረስ ለህዝብ ጉብኝት ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡