የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም (PIDA Week) ተሳታፊዎች የ“ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ኤግዚቪሽንን ጎበኙ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን ጎብኚዎችን በተቀበሉበት ወቅት የ“ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024” ኤግዚቪሽን በአረንጓዴ ትራንስፖርት ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የግንኙነትና የትብብር እድሎችን ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችውን እንቅስቃሴ ለማሳካት በበርካታ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ብለዋል ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን፡፡

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጭነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቁ በየአመቱ በርካታ ችግኞችን በመትከል የዓለም ስጋት የሆነውን አየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን በካይ ጋዝ ሙሉ ለሙሉ በሚያስቀር መልኩ ታዳሽ የኃይል ምንጭን ጥቅም ላይ በማዋል አረንጓዴ ትራንስፖርትን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና በዘርፉ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ዘርፉን ዘላቂነት በሚያረጋግጥ መልኩ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እናደርጋለን ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት የታክስ ማበረታቻዎችን በማድረግና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ በቅርብ በመደገፍ ለአረንጓዴ ትራንስፖርት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም (PIDA) ተሳታፊዎች በኤግዚቪሽኑ የቀረቡ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የብዙሃን ትራንስፖርት፣ የግል አውቶሞቢሎች፣ የመለስተኛ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ብስክሌቶችና ሌሎችም አነስተኛ የአረንጓዴ ትራንስፖርት አማራጮችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም (PIDA WEEK) በትራንስፖርት፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች፣ በኃይል አቅርቦትና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚመክር የዘርፉ ሃላፊዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ስምንተኛው ጉባኤ “PIDA WEEK” ከህዳር 16/2017 ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡

Share this Post