የኢ-ሞቢሊቲ ስትራቴጂው ወደ አረንጓዴ ትራንስፖርት የምናደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው” – ክቡር አቶ በረኦ ሀሰን
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት፣ የልማት አጋሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የግል ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በረኦ ሀሰን ስትራቴጂው በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ ከብክለት የፀዳ እና ቀልጣፋ የትራንስፖርት ስርዓት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በአረንጓዴ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል መሙያ መሰረተ ልማት እና በተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በአፍሪካ ግንባር ቀደም ሀገር መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከትራንስፖርት ዘርፍ የሚወጣውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ ውጤታማ እርምጃዎች በተግባር እየተወሰዱ መሆኑን አብራርተዋል።
ለህዝብ ትራንስፖርት የሚያገለግሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤሌክትሪክ አውቶቢሶች ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፁት ሲሆን፣ በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል መሙያ ጣቢያዎች በስፋት እየተገነቡ መሆኑንም አስረድተዋል። ይህም በርካታ የስራ ዕድሎችን እየፈጠረ መሆኑ ተጠቁሟል።
እንዲሁም ሀገሪቱ በታዳሽ ሃይል ላይ ትኩረት በማድረግ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎችን እያዘጋጀች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ስትራቴጂውን በተግባር ለማዋል እየሰራች መሆኑን ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የኢ-ሞቢሊቲ ስትራቴጂውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት በሚደረጉ ተግባራት ዙሪያ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ክቡር አቶ በረኦ ሀሰን መንግስት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስርዓት ልማት ላይ እየወሰዳቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን አብራርተዋል።