አፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት የቀጠናው ሀገራትን በመንገድ እና በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር ት የጋራ ብልፅግና ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገለፀ።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢ/ር እህታየሁ መሰለ በ2017 በጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን የማሟላት፣ በደወሌ፣ ደቼቶ እና በአዋሽ የጭነት ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ተርሚናል ግንባታ የቅድመ ዝግጂት ስራዎች፣ የቀዝቃዛ መጋዘን ግንባታ የቅድመ ዝግጂት ስራዎች፣ የሀገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት በባሮ ወንዝ ላይ ለማስጀመር የተሰሩ ስራዎች፣ ከሁለት ሺህ በላይ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ስልጠና የተሰጠ ስለመሆኑ እና የመልቲ ሞዳል ኦፕሬተሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ መሠራቱን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ደንጌ ቦሩ ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በመንገድ እና በመሠረተ ልማት ትስስር እንዲኖር በማድረግ የጋራ ብልፅግና ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

በቅርቡ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የመኢሶ ድሬደዋ የፍጥነት መንገድ የዚህ ፕሮጀክት አካል በመሆኑ ፕሮጀክቱ በጅቡቲ ኮሪደር በኩል ያለውን የሎጅስቲክስ እና ንግድ ስርዓት የተሳለጠ በማድረግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው ሲሉ ክቡር ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል።

በጅቡቲ ኮሪደር በጭነት አሽከርካሪዎች በኩል በመሰረተ ልማትና የፋሲሊቲ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል የተናገሩ ሲሆን የሀገሪቱን ሎጂስቲክስ ለማሻሻል አሰራሮች ዲጂታላይዝ የማድረግ እና በዘርፋ የሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲኖር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ያስሚን ውሀብረቢ በበኩላቸው የሀገሪቱ የኤክስፖርት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ አያደገ መሆንን የገለፁ ሲሆን ፕሮጀክቱ የሎጂስቲክስ ዘርፍን ለማሻሻል ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በግምገማው ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ፣የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማት የሆኑት ኢትዮ- ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አ.ማ እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣንን ጨምሮ የተለያዩ የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post