ሀገር ውስጥ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሰረተ ልማት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ከአንጎላ ለመጡ ልዑኳን ቡድን ተሞክሮ አጋሩ።
ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (ትሎሚ):-ሀገር ውስጥ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና መሰረት ልማት ላይ የተሰማሩ የኢትዮ- ቴሌኮም፤ ቬሎ ሲቲ ባስ (ግሪን አዲስ) እና ቢኬጂ (BKG) ከአንጎላ ለመጡ የትራንስፖርት ዘርፍ ልዑካን ቡድን ተሞክሮ አጋርተዋል።
ሉዑኳን ቡድኑ ከአንጎላ ሀገር ትራንስፖርት፣ አካባቢ ጥበቃ እና አነርጂ ዘርፍ የተወጣጡ ሲሆን በኢትዮጵያ እየተተገበሩ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ እና የቻርጂ ስቴሽን መሰረት ልማትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በተሞክሮ ልውውጡ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን በመንግሥት እና በግል አጋርነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አብራርተዋል።
ሞተር አልባ ትራንስፖርት ሽግግር፤ ዲጂታል የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ውጤታማ የሆነ የነዳጂ አጠቃቀም፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የብዙሃን ትራንስፓርት ማስፋፋት፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ክቡር ሚኒስትር ደኤታው ለሉዑኳን ቡድን ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
ሚኒስትር ደኤታው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና መሰረተ ልማቱ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድልም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የሉዑኳን ቡድኑ አባላት በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማስፋፋት በመንግሥት የተወሰዱ የፓሊሲ አቅጣጫዎች፤ የመንግስትን እና የግል ዘርፋን ቅንጂታዊ አሰራር ፤ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ያደነቁ ሲሆን አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የእርስበርስ ልምድ ልውውጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ልዑካኑ በአራት ቀናት በነበራቸው ጊዜ በአዲስ አበባ የመስክ ምልከታ በማድረግ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራዊ ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን በዛሬው እለት በተደረገው ውይይት ቆይታቸው ተጠናቋል ።